አሰልጣኞች በተጨዋቾቻቸው ላይ ተመስርተው የጨዋታ ታክቲክና ፎርሜሸን መንደፍ አለባቸው? ወይስ የሚፈልጉትን ታክቲክና ፎርሜሽን ባሉት ተጫዋቾች ላይ መተግበር አለባቸው?

አሰልጣኞች በተጨዋቾቻቸው ላይ ተመስርተው የጨዋታ ታክቲክና ፎርሜሸን መንደፍ አለባቸው? 

ወይስ የሚፈልጉትን ታክቲክና ፎርሜሽን ባሉት ተጫዋቾች ላይ መተግበር አለባቸው?


አሰልጣኞች በተጨዋቾቻቸው ላይ ተመስርተው የጨዋታ ታክቲክና ፎርሜሸን መንደፍ አለባቸው ወይስ የሚፈልጉትን ታክቲክና ፎርሜሽን ባሉት ተጫዋቾች ላይ መተግበር አለባቸው?

ይህ ጥያቄ የበርካታ የእግርኳስ ባለሙያዎች መከራከሪያ ሲሆን ደጋግመን አይተናል። አንዳንዶቹ የአሰልጣኙ የጨዋታ ፍልስፍናና የፍላጎት ነፃነት መከበር አለበት ሲሉ ሌሎች ደግሞ አሰልጣኝ ማለት ካሉት ተጫዋቾች ላይ የመጨረሻውን ምርጥ ብቃት አውጥቶ መጠቀም ነው፤ ስለዚህ በቡድን ውስጥ ላሉት ተጫዋቾች የሚሆን ታክቲክና ፎርሜሽን መነደፍ አለበት እያሉ ይከራከራሉ።

አሁን በቶተንሃም የሚሰሩት የቀድሞው የፖርቶና ቼልሲ አሰልጣኝ አንድሬ ቪያሽ ቦኣሽ ለአማካዩ የቀረበ የተከላካይ መስመር high defensive line እና 4 - 3 – 3  በጣም ይወዱ እንደነበረ በተደጋጋሚ ተስተውሏል። ፍቅራቸው እንዲያውም ውጤት እስከማሳጣት ደርሷል። አንዳንዴ እንዲያውም 9 ቁጥር ተጫዋቹን ቶሬስ ጭምር ዊንገር አንድርገው እስከማጫወት ደርሰው ነበር።         

                           
       ፖርቶ በአንድሬ ጊዜ                                           ቼልሲ በአንድሬ ጊዜ 

ይህ አካሄድ በተደጋጋሚ ሲያስተቻቸው ነበር። የሆኖ ሆኖ ታክቲክ ና ታክቲክ አጠባበቅ የዘመናዊ ቡድኖች መገለጫ ከሆነ ቆይቷል። የአንድ ቡድን ተጫዋች በጣም ጎበዝ ይሁን እንጂ ለአሰልጣኙ ና ለጨዋታው ታክቲክ ካልመጠነ አሁን አሁን ብዙም አይፈለግም ምንም እንኳ ነፃ ሚና የሚሰጣቸው ተጫዋቾች ቢኖሩም።

የጨዋታንና የተጫዋቾችን ዝብርቅርቅነት ስርኣትና ቅርፅ ማስያዝ ነው የታክቲክ ሚና። አንዳንድ ቡድኖች ግን በታክቲክ ብቻ ታጥረው ተመልካቹን ሳያዝናኑ ይወጣሉ።

ግን አንድ እውነት ሳይኖር አይቀርም። ታክቲክ የሚባለው ነገር የእግርኳስን የመጨረሻ ኢላማን አያስመታም። ቡድኖች በታክቲክ ቢሳካላቸውም ጎል በጣም ሲያስፈልጋቸውና  ወይም ያገቡትን ጎል ለማስጠበቅ በጣም ሲፈልጉ ታክቲክ የሚባለው ነገር አሰልጣኞች አይምሮ አይመጣም። በቀውጢ ሰኣት ታክቲክ የሚባል ነገር የለም። ይህን ስል ግን ታክቲክ ብለው ይዘውት የገቡትን ይተዉና ኳሱን ዝም ብሎ ወደተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ መጣልን የደመነፍስ ታከቲክ ያደርጉታል ማለቴ ነው 

ባለፈው አመት በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ ቀን ማንቼስተርሲቲ ከኪፒአር ሙሉ 3 ነጥብ ይፈልግ ነበር። ያ ግን እስከመጨረሻው ሊሆን አልቻለም። የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ግርግር ነበሩ ማለት ይቻላል። ተከላካይ የሚባል የለ በሙሉ አጥቂ ሆነ ፤ ያ ግርግር ግን መጨረሻው የሚፈልገውን ነገር አገኘ። ሲቲ 3 ለ 2 አሸንፎ ዋንጫውን አነሳ።

ባለፈው ማክሰኞ በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ሩብ ፍፃሜ ቦሩሲያ ዶርትሙንድ በማላጋ 2 ለ 1 እየተመራ ነበር ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃ እስኪቀረው። የመጨረሻዎቹ ጥቂት ደቂቃዎች ግርግር ግን ዶርትሙንድን 3 ለ 2  አሸናፊና ወደ ግማሽ ፍፃሜ አላፊ አደረገው። ዶርትሙንድ ሁለት ጎል ፍለጋ የመጨረሻዎቹን ደቂቃዎች ሲራወት ታክቲክ የሚባል ነገር አልነበረም ፤ ራሳቸውን ለመልሶ ማጥቃት ፍፁም አጋልጠው ነበር የሚጫወቱት። ማላጋ ደግሞ በበሰለ ታክቲክ እስከመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ድረስ ሲከላከል ነበር። የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ግን መከላከሉን ግርግር አደረጉበትና ጉዞው ሁሉ ከሸፈ ፤ እንደብረት ሲከላከሉ የነበሩት እነ ዲሜኬለስ ተወናበዱና ሁሉም ነገር ከሸፈ። የማላጋ ተጫዋቾች እስከመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ድረስ የዶርትሙንድን ተጫዋቾች ከጨዋታ ውጭ ሲያደርጉ የነበረበት ብስለትም አስገራሚ ነበር። መጨረሻ ላይ ግን ያሁሉ ሊሆን አልቻለም።

በጨዋታ ታክቲክ እና በተጫዋቾች መሃል ያለው ዝምድና ቀጥተኛ ነው። በታክቲክ ብቻ የሚጫወት ቡድን ሁሌም ውጤታማ አይሆንም። ተጨዋቾች ለታቀደው ታክቲክ የሚሆን ስሜትና ፍላጎት ከብቁና ተጣጣፊ አካል ብቃት ጋር መያዝ አለባቸው። የፈለገ የበሰለ ታክቲክ የሚነድፍና ሜዳ ላይ ቡድን የሚቀያይር አሰልጣኝ ቢኖር ተጫዋቾቹ ለዛ ታክቲክ መተግበር የሚሆን አካል ብቃትና የአይምሮ ብቃት ከሌላቸው ከባድ ነው። እዚህ ጋር የጃፓኖችን ምሳሌ ልጥቀስ! ጃፓን በ 2010 ሩ የአለም ዋንጫ ና በቅርብ አመታት ውድድሮች የሚገርም ኳስ ቅብብል ፤ የባርሰሎና ተፅእኖ ያለበት ጨዋታ ትጫወት ነበር። ጨዋታው ግን እንደባርሰሎና ተጋጣሚን አያስከፈትም። ለምን ቢባል እንዲሁ በስልጠናና በታክቲክ ትምህርት የመጣ ጨዋታ እንጂ ከስሜት ከደመነፍስ ከተሰጥኦ የመጣ ስላልሆነ ነው።

ታዲያ ታክቲክ ለጨዋታ ምኑ ነው?  ታክቲክ ማለት የጨዋታ የበላይነትን ለመወሰን የሚያስችሉትን የጎል እድሎች ጉዳይ በቀጥታ መወሰን ማለት ነው። ምን ያህል ጥራት ያላቸው የግብ እድሎች ይፈጠራሉ የሚለውን ታክቲክ ይወስናል። ጥራትና ብዛታቸውን!

የሚፈጠሩትን የግብ እድሎች መጠቀም ላይ ግን ታክቲክ ቦታ የለውም። ይህ የተጫዋቾች ስራ ነው። ግን ታክቲኩን የሚወስኑትና የሚነድፉት አሰልጣኞቹ ናቸው።  ይህ ማለት በግርድፉ አሰልጣኞቹ የጎል እድል ይፈጥራሉ ፤ ተጫዋቾች ሊያገቡም ላያገቡም ይችላሉ፤ ያገባ እና በጎል የበለጠ ቡድን ግን ሁሌም ያሸንፋል።

ስለዚህ በማሸነፍና ባለማሸነፍ መሃል ያለው የአሰልጣኞች ስራ ተጫዋቾችን በአካልና በመንፈስ ማብቃት ወይም ብቁ የሆኑትን መምረጥ ብቻ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል።
ይህን ለማብራራት ያህል ሌላ ጥያቄ እናንሳ! የጨዋታ ውጤት ጨዋታን ይናገራል ወይስ አይናገርም?

ይናገራል የሚል መልስ ከተሰጠ ፤ ታዲያ ተመልካቾች ለምን ጨዋታው ሊያልቅ ሲል ብቻ ስቴዲየም አይገቡም? ውጤቱን ብቻ አይተው ለምን አይሄዱም?  በስፔን እግርኳስ በጣም ወጣቱ የላሊጋ አሰልጣኝ ሁኣን ማኑኤል ሊዮ ነው። በ 29 አመቱ ሳላማንካን በ 1993 ለላጊው አብቅቶ ነበር። ሊዮ አሰልጣኝነትን የጀመረው ግን ገና በ 16 አመቱ ነበር። አሁን አለም ላይ ታላላቅ ቡድኖች የሚጠቀሙትን 4–2–3–1  የተባለውን ፎርሜሽን በስፔን ና በመላው አለም ዝነኛ እንዲሆን ከ 1990ቹ መጀመሪያ ጀምሮ ሲያስተዋውቅ የነበረው ሊዮ ፤ ከሳላማንካ ስኬቱ ወዲህ ግን ብዙም ሳይሳካለት ያለፉትን 20 አመታት አሳልፎ አሁን 50 አመት ሊሞላው ጥቂት ነው የቀረው። 

ሊዮ ከቢልዛርድ መፅሄት ጋር ቆይታ ሲያደርግ ውጤት ቁጥር ነው ይላል። የስፖርት ጋዜጠኞችን የስፖርት ጋዜጠኛ ያደረገው ውጤት መንገር ሳይሆን ውጤቱ የመጣበትን ሂደት ማብራራታቸው ነው ይላል። በስፖርት ውይይት ፕሮግራም ላይ ሰዎች የሚከታከሩት ውጤትን ሳይሆን ውጤቱ የመጣበትን ሂደት ነው። ስለዚህ ውጤት ጨዋታን አይገልፅም ይላል።

ከላይ የገለፅነውን አሰልጣኝ የጎል እድል ይፈጥራል ፤ ተጫዋቾች ያገባሉ ወይም አያገቡም ያልነውን መነሻ በማድረግ አሰልጣኞች ይወቀሱ ወይስ አይወቀሱ የሚለውን መረዳት ይቻላል። አሰልጣኞችን ለመውቀስ ውጤትን መነሻ ማድረግ ሳይሆን ውጤቱ የመጣበትን እንቅስቃሴ ማየት የግድ ሳይሆን አይቀርም። እንደ ሊዮ መደምደሚያ ሰዉ የሚወቅሰው በመጥፎ ሁኔታ የተሰራውን ቡድን ሳይሆን መጨረሻው መጥፎ የሆነውን ቡድን ነው፤


የሆነ ሆኖ ተጫዋቾችም ያለ ታክቲክ፤ ታክቲክም ያለ ተጫዋቾች የትም አይደርስም። ለዚህም ነው እኛ እዚህ ሲጫወት ጎበዝ የመሰለን ተጫዋች ሌላ ቦታ ሲሄድ ጎበዝ የማይመስለው።  

Post a Comment

Previous Post Next Post