ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ የርስበርስ ጦርነቶች ድሮኖች ምን ያህል ሚና ኣላቸው?

ኢትዮጵያ ውስጥ ለድሮን የሚበቃ ኢላማ ማለትም ከባድ መሳሪያና መሰረተ ልማት ያለው መንግስት ራሱ ነው። እንደ ህወሃት መደበኛ ሰራዊት ያለው ቡድንም የለም። ድሮኖች በህወሃት ጦር ላይ ያደረሱትን ያህል ኪሳራ በፋኖ ወይም በኦነግ ሰራዊት ላይ ማድረስ ኣይችሉም!


ድሮን ሰው ኣልባ ኣውሮፕላን ማለት ነው። በርቀት መቆጣጠሪያ ከምድር ይዘወራል። ኢትዮጵያ ውስጥ ሰው ስለ ድሮኖች በሰፊው ማውራት የጀመረው በህወሃትና በኣብይ ኣህመድ መንግስት መካከል ጦርነት ከፈነዳበት ጊዜ በኋላ ነው። በትዕቢትና በንቀት የኣብይ መንግስት ወታደሮችን በተኙበት በመጨፍጨው የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት የጀመሩት ህወሃቶች ከመንግስት ሰራዊት የዘረፉት ከባድ መሳሪያ በድሮን መቀጥቀጥ ሲጀምር ድሮኖቹ ምን እንደሆኑ እንኳ ባለማወቃቸው የፋሽስቱ ኣብይ ሰራዊት ኣፍሪካ ውስጥ በሌሉ ውስብስብ መሳሪያዎች የትግራይ ህዝብን እየጨፈጨፈ ነው ይሉ ነበር በሚዲያቸው። 

መሳሪያዎቹ ድሮን መሆናቸው ከታወቀ በኋላ በመጀመርያው ዙር ጦርነት የደረሰባቸውን ሽንፈት በድሮን ኣሳብበዋል። 

ባለሙያዎች እንደሚሉት በየትኛውም ኣይነት ጦርነት በሽምቅም ይሁን በመደበኛ የፊት ለፊት ውጊያ ድሮኖች ብቻቸውን የሚቀይሩት ምንም ነገር የለም። በተለይም ዋጋቸው ርካሽ የሆኑ ከቱርክ ከኢራን ከመሳሰሉ ኣገራት የሚገዙ ድሮኖች የኣነጣጣሪነት (Precision) ኣቅማቸው ኣናሳነት እንዲሁም በቀላሉ በኤሌክትኖኒክ ስ ህበት ግንኙነት የመጠለፍ (jammed የመሆን) ዕድላቸው ከፍተኛነት ጦርነትን የመቀየር ኣቅማቸውን ዝቅተኛ ያረጋዋል። የሆኖ ሆኖ የኢትዮጵያ መንግስት የታጠቃቸው ድሮኖች በመደበኛ የፊት ለፊት ውጊያና በሽምቅ ውጊያ ላይ ሊኖራቸው የሚችለውን ሚና እንመልከት።

መደበኛ የፊት ለፊት ውጊያ

እንደዚህ ኣይነት ውጊያዎች የሚደረጉት ተመጣጣኝ ኣቅምና ትጥቅ ባላቸው ኃይሎች መካከል ነው። በሰሜን ኢትዮጵያ በመጀምርያ ዙር የተደረገው ጦርነት መደበኛ ውጊያ ነበር። ህወሃና የኣብይ ኣህመድ መንግስት ተመጣጣኝ የሰው ኃይልና ከባድ መሳሪያ ይዘው ነው ጦርነቱን ያደረጉት።

በዚህ ውጊያ የኣብይ ሰራዊት የታጠቃቸው ድሮኖች የህወሃትን ከባድ መሳሪያዎችና የተወሰኑ ኣመራሮቹን በመምታት ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። በዚህ ጦርነት ድሮኖች ሊወጡት የሚገባውን ሚና በአግባቡ ተወተዋል ማለት ይቻላል። 

ባለሙያዎች እንደሚሉት ድሮኖች በዋነኝነት ሶስት ስራ ይሰታሉ። ኣንዱ ስለላ ነው ። ሁለተኛው የተመረጡ ኢላማዎች ላይ ቦምብ መጣል ወይ ራሳቸው በመፈንዳት ኢላማውን ማጋየት ሲሆን ሶስተኛው ደግሞ የጠላትን የኣየር ኃይል በብዛት በመግባት ማጨናነቅ ነው።

በዚህ መሰረት የህወሃትን ከባድ መሳሪያዎችና ሁለት ኣመራሮቹን በመግደል ሁለተኛውን ሚና በቂ በሚባል ደረጃ ተወተዋል። ሆኖም ህወሃት ከመቀሌ ሲወጣና ጦርነቱ ጠላትን በስስ ጎኑ እየገቡ ኣዳክሞ የማሸነፍ (war of attrition) የሽምቅ ውጊያ ሲሆን የድሮኖቹ ሚና ዜሮ ገባ። በህዳር መቀሌን የተቆጣጠረው የመንግስት ሰራዊት በስድስት ወር ውጊያ ተዳክሞ የውጊያ መኮንኖቹን ሁሉ ኣስጨርሶ በሽንፈት ከትግራይ ወጣ። ከትግራይ መውጣት ብቻ ኣይደለም እየሸሸ መቶ ጦርነቱ ደብረብርሃን ደረሰ።

በሩስያና በዩክሬይን ጦርነት ዩክሬን የቱርኩን ባይካር ድሮኖች በመጠቀም በርካታ የሩስያ ታንኮችን እንዳወደመች ሲነገር ነበር። ሩስያ በበኩሏ በርካታ የኢራን ሻሂድ ድሮኖችን ወደ ዩክሬይን የአየር ቀጠና በማስገባትና የኣየር መከላከያውን በማጨናነቅ ረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤሎቿ በዩክሬይን የኤነርጂ መሰረተ ልማቶች ላይ ከባድ ጉዳት ኣድርሰዋል ይባላል። በቅርቡ ደሞ ዩክሬይን በሩስያ ዋና ከተማ ማስኮና በክራይሚያ ድልድል ላይ ጦርነቱ ላይ ምንም ተጽዕኖ የማያሳድሩ ጥቃቶችን ፈጽማለች። ኣላማው የስነ ልቦና ተጽዕኖ ማድረግ እንደነበረ ራሳቸው ዩክሬኖች ተናግረዋል። ይህ የሚነግረን ነገር ድሮኖች ሚሳኤሎችን ለመሳሰሉ ሌሎች ከባድ መሳሪያዎች ደጋፊ ከመሆን በዘለለ በተራዘመ ጦርነት ውስጥ ያላቸው ሚና ኣናሳ መሆኑን ነው። 

ሕወሃት ደብረ ብርሃን ከድረሰ በኋላ የመንግስት ጦር ባደረገው መልሶ ማጥቃት ወደ ትግራይ ሲመለስ ድሮኖች በጭነት መኪናና በኣገር ኣቋራጭ አውቶቡስ ተጭነው ሲመላለሱ የነበሩ ታጣቂዎቹን እየተከተሉ በመምታት ትልቅ ሚና ነበራቸው ይባላል። ሆኖም የመንግስት ጦር ሰሜን ወሎን ከህወሃት ለመንጠቅ ከባድ መስዋትነት እንደከፈለ ነው ሚነገርው። ድሮኖች ለኣጭር ጊዜ ዘመቻ ካልሆነ በቀር ወሳኝ የፊት ለፊት ውጊያ ላይ ምንም ሚና የላቸውም ፥ ሚናው የከባድ መሳሪያና የዕግረኛ ሰራዊት ይሆናል። በመጨረሻው ዙር ጦርነት ድሮኖች የህወሃት ባለስልጣናትን ለመግደል ያደረጉት ሙከራ ኣንዱም ኣልተሳካም።

ሽምቅ ውጊያ

የተራዘመ ሽምቅ ውጊያ ላይ ድሮኖች በስለላና የተመረጡ ኢላማዎች በመምታት ወይም የውጊያ መሪዎችን በመግደል ግዳጅ ይወጣሉ::

ኦሮምያ ውስጥ ካሉ ታጣቂዎች ጋር በሚደረገው ውጊያ ድሮን የተጠቀመው ኣንድ ግዜ ብቻ ነው። ይህም የታጣቂዎቹን የምርቃት በአል ላይ በመተኮስ ብዙ ሰው እንደገደለ ተዘግቧል። ሆኖም የኦሮምያ ታጣቂዎች ለድሮን ጥቃት የሚበቃ ኢላማ ከባድ መሳሪያ ስለሌላቸው በዚህ ውጊያ ድሮን ተፈላጊ ሊሆን ኣልቻለም። የኦሮምያ ታጣቂዎችም ቁጥራቸው እየበዛ የሚንቀሳቀሱበት ቦታ እየሰፋ ነው የመጣው።

የታጣቂዎቹ መሪ ጃል መሮም በተደጋጋሚ በድሮን ተመቷል ቢባልም ዜናው ሁሉ ውሸት ሆኖ ቀርቷል። 

በኣማራ ክልል በተጀመረው የመንግስትና የታጣቂ ፋኖዎች ውጊያ ገና ካሁኑ ድሮን ጥቅም ላይ መዋሉ እየተነገረ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ኣብይ ለተቃዋሚዎቻቸው "ውጊያን በቴክኖሎጂ (በድሮን) ነው የምናረገው የምንጨርሰው ደግሞ በኮማንዶዎቻችን ነው" ካሉ በኋላ ነው ጥቃቱ የደረሰው። 

የቱርክ ድሮኖች እስከ ሁለት ሚሊየን የኣሜሪካ ዶላር ሲያወጡ የኢራኖቹ እስከ ሃያ ሺህ ዶላር ድረስ ይረክሳሊ ይባላል ፥ ሆኖም ኣሜሪካ ያላትን ያህል ከፍተኛ አነጣጣሪነት (precision) ብቃት ያላቸው ድሮኖች የታጠቀ ኣገር የለም ይባላል። እነዚህን ድሮኖች በመጠቀም የኣቃኢዳውን መሪ በካቡል ኣንድ መንደር ውስጥ በክፍል ውስጥ ገላዋለች። 

ኢትዮጵያ ውስጥ ለድሮን የሚበቃ ኢላማ ማለትም ከባድ መሳሪያና መሰረተ ልማት ያለው መንግስት ራሱ ነው። እንደ ህወሃት መደበኛ ሰራዊት ያለው ቡድንም የለም። ድሮኖች በህወሃት ጦር ላይ ያደረሱትን ያህል ኪሳራ በፋኖ ወይም በኦነግ ሰራዊት ላይ ማድረስ ኣይችሉም። ኣስርና ሃያ የማይሞላ ሰው ወይም ታጣቂ ለመግደል ብሎ መንግስት ድሮን ካዛመተ ወጪው ከጥቅሙ ያመዝናል ፤ ኣያዋጣውም::

እነ ኣሜርካ ከርቀት በባዕዳን ኣገር ያሉ የተመረጡ ኢላማዎችን ለዚያውም ውድ በሆኑ ድሮኖች ለመምታት የሚጠቀሙትን የውጊያ ስልት የኢትዮጵያ መንግስት በተቃዋሚዎች ላይ ለመጠቀም መወሰኑ ምን ያልክ ከዕውነታ የተጣላ መሆኑን ያመላክታል የሚሉ ኣሉ።

ድሮኖች ለኣጭር ግዜ ኦፐሬሽን ጥቅም ላይ ይውሉ ይሆናል። የተራዘመ የማዳከም ጦርነት ግን በድሮን ሃይል ኣያልቅም። የወታደር ቁጥር ፥ ስንቅ ፤ የመዋጋት ሞራል ፥ ማህበረሰባዊ ሃላፊነት ወዘተ ናቸው የጦርነቱን ኣሸናፊ የሚወስኑት። ዕራስህ የምትመራውን የገዛ ኣገር እንደ እስራኤልና ኣሜሪካ ከርቀት በድሮን መትቼ ካልሆነ በጭለማ ከሄሊኮፕተር ኮማንዶ ኣዝንቤ እቆጣጠራለው ማለት እብደት ነው። ምናልባት እስከተወሰነ ግዜ የአዲስ ኣበባ ንጉስ ኣድርጎ ሊያስቀጥ ይችላል ፥ ኢትዮጵያን የሚያክል ሰፊ ኣገር ግን መግዛት ኣያስችልም።

ኢቶጵያ ውስጥ ድሮኖች ጥቅም ላይ የሚውሉት መቀሌ ኣንዣበው ይመለሱ እንደነበረው ለማስፈራራትና ብዙም ስለ ድሮን እውቀት የሌለውን ምስኪን ህዝብ ፈርቶ ለማስቀመጥ ካልሆነ በቴክኖሎጂ እጨርሳችዋለው ብሎ ህዝብ ማስፈራራት የትም ኣያደርስም። ከኦነግ ሰራዊትም ሆነ ከፋኖ ጋር ያለው ውጊያ በሰላማዊ ንግግር ብቻ ነው ሊፈታ የሚገባው::

Post a Comment

Previous Post Next Post