ሴቶች ያረጃሉ ፤ ወንዶች አያረጁም ባይባልም እንደሴቶች ግን አይደለም። ካልተወደደች በቤተሰቦቹ ጫና ፤ በእሷ እድሜ መግፋት እና አማላይነት መቀነስ ምክንያት ሊተዋት የሚችልበት እድል ሰፊ ነው

የባሌ ዘመዶች ቤት ምን ይዤ እንደምሄድ ጨንቆኛል! ብለሽ ይሆን



በእኛ አገር ባህል ለፍቅር ተጓዳኝ ቤተሰቦች ከፍተኛ ክብር ይሰጣል። ልጅቷ ቀድማ ብትወጣም ወንድየዋ መቼም ቤተሰቦቿን እንደው ለይስሙላ እንኳ ሳያስፈቅድ አይወስድም። የወንዱም ነገር ያው ነው። ሴቷ የወንዷ ቤተሰቦች ካልወደዷት ምንም እንኳ እሱ ቢወዳትም ህይወቷ በተወሰነ መልኩ አስቸጋሪ መሆኑ አይቀርም። ሴቶች ያረጃሉ ፤ ወንዶች አያረጁም ባይባልም እንደሴቶች ግን አይደለም። አርጅተውም ወጣት እንስቶችን የሚያገቡ ወንዶች ብዙ ናቸው። ያረጀችን ሴት የትኛው ወንድ ይፈልጋታል? ይሄ ከባድ አባባል ቢሆንም ግን የብዙ ተጓዳኞች እውነታ ነው። እናም ሴት ልጅ በወንድ ጓደኛዋ ቤተሰቦች መወደድ የግድ የሚባል ነገር ነው። ካልተወደደች በቤተሰቦቹ ጫና ፤ በእሷ እድሜ መግፋት እና አማላይነት መቀነስ ምክንያት ሊተዋት የሚችልበት እድል ሰፊ ነው። የሞራል ልክነት ባይኖረውም። ስለዚህ ለመወደድ ደግሞ አንዱ አጋጣሚ የበአል ሰሞን አጋጣሚ ነው።

ብዙ ሴቶች በወንድ ተጓዳኛቸው ቤተሰቦች እንዴት መወደድ እንዳለባቸው ይጨነቃሉ። ጭንቀቱ ከላይ በጠቀስነው የጋራ መግባቢያ መሰረት ልክ ነው። ለመወደድ አንዱ አጋጣሚ በበአል ሰሞን ለእርስ ቤተሰብ የምታሳዪው ቅርበት ነውና ትልቅ ጥንቃቄ ይጠይቃል። ኬክ ይዘሽ ሄደሽ ምን ነክቷት ነው እንዳይሉሽ ተጠንቀቂ። አንተም የሚስት ዘመዶች ጋር ስላለህ ግንኙነት ማሰብ ይጠይቃል። ለሁለታችሁም የሚሆን የበአል ቁምነገር አለን እና አንድ በአንድ አንብቡን። በሴት ይፃፍ እንጂ ላንተም ይሆናል።  

ጆሮሽ እና አይንሽ ይከፈት ብዙ ተጓዳኞች ለተጓዳኛቸው ወላጆች ብዙ ትኩረት አይሰጡም። ትኩረት ሲባል በየወሩ ገንዘብ እየቆረጡ መስጠት አይደለም። እውነተኛው ትኩረት የስሜት እና የመከባበር አንድነት ነው። ለበአል የባልሽ ቤተሰቦች ጋር የምትሄጂው ዞረሽ ፤ ዞረሽ ማታ ሲመሽ ከሆነ ጥሩ አይመጣም። ጊዜ ልትሰጫቸው ያስፈልጋል። አርጅተዋል እና ብዙ እነሱን ማናገር አያስፈልግም ብለሽ ካሰብሽ ተሳስተሻል። የባልሽ አባት የድሮ ሰው ስለሆነኑ ምናልባት የድሮ የበአል ታሪክ ነግረው ያሰለቹኛል አትበይ። እቤታቸው ሄደሽ ልክ እንደባልሽ ልጃቸው ነኝ ብለሽ ወይም አስመስለሽ አጠገባቸው ተቀምጠሽ አጫውቻቸው። አይንሽ ከፊታቸው ላይ አይነቀል። ማንኛውም ሰው ትኩረት ይፈልጋል። ትኩረት እንደምትሰጫቸው ሊያውቁ ይገባል። ጆሮሽን ሰተሽ ስሚያቸው! የፈለገ አሰልቺ የድሮ ነገር ወይም አይረባም ብለሽ ብታስቢም የመሰላቸት ፊት አታሳዪ። የበአል ቀን ትልቁ ስጦታ እንደተለመደው በግ ይዞ መሄድ ብቻ ሳይሆን ትኩረት እና ክብር ነው። የባልሽ አባት እንደ ባሌ ነው የማያቸው ብለሽ በትንሹ እራስሽን ልታሳምኚው ይገባል ፤ ደግሞም ነው። ስለዚህ ጆሮሽና አይንሽ ተከፍቶ ይሰጣቸው። በጣም ይወዱሻል። “ልጃችን ምንኛ ታድሏል ይህቺህ የሴት መልአክ በማግባቱ” ይላሉ። አራዳ ከሆንሽ ነገሩ እንደዚህ ነው።


በእኛ አገር ባህል ብዙ ግዜ የባል እናቶች የልጃቸው ሚስት ላይ ይቀናሉ ወይ ደግሞ እነሱ እንደሚፈልጓት እንድትሆን ይፈልጋሉ የሚባል አባባል አለ። አንቺ ግን ይህን በራስሽ ብልጠት ማሰኬድ ይችያለሽ። የበአል ሰሞን ደግሞ ለዚህ ትክክለኛው አማራጭ ነው ፤ አጋጣሚ ነው።    

እቤታቸው ብታድሪስ? በአል ከአንድ ቀን ያልፋል። ዋዜማው ፤ የበአሉ ቀን ፤ ማግስቱ ወዘተ በአልን ያረዝሙታል። ከቻልሽ አንቺ ከዋዜማው ጀምሮ አብረሻቸው ብትሆኚስ? ምንም ማለት አይደለም። በጉን ፤ ዶሮውን ፤ ቅቤውን አብረሽ እንደ ልጃቸው ብታጋዣቸው የአብሮነት ፤ የአንድነት ስሜት ይሰጣቸዋል። እናቱን የበአል ምግብ በመስራት ብታግዣቸውስ? ይሄም ካሰብሽበት ብዙ አይከብድም። እራሱ አመት በአል ማለት እኮ ለየት ያለ ፤ ከተለመደው ቅዳሜ እና እሁድ የተለየ ማለት ነው። ላንቺም የተለየ ድባብ መፍጠር ነው ፤ በሌላ ጎኑ ደግሞ ከባልሽ ዘመዶች ጋር ያጣብቅሻል።

ይህን ማድረግሽ ትላንት የመጣችዋ የልጄ ሚስት ሳይሆን የሚያስብልሽ ረጅም አመት አብረሻቸው እንደኖርሽ ሴት ልጃቸው እንዲያስቡሽ ፤ እንዲወዱሽ ነው የሚያደርገው።  

ቆንጆ የበአል ስጦታ ፈልገሽ ስጫቸው   ስጦታ ማለት መንገድ ላይ የተዘረጉት ካርዶች አይደሉም ፤ ወይም ከገበያ እየጎተትሽ የምታመጪው በግ አይደለም። ስጦታ ሲባል ደብቀው የሚያስቀምጡት ፤ ታሪኬ ብለው የራሳቸው ስብስብ ውስጥ የሚያካትቱት ማለት ነው። በአንድ ወቅት የአንድ ጓደኛችን ሚስት ያደረገችው ነገር ለሁላችንም ቆንጆ ትዝታ ሆኖናል። የልጅቷ ባል አባት ከወጣትነት ጊዜያቸው ጀምሮ ቴኒስ መጫወት የሚወዱ ሰው ናቸው። አሁንም ቅዳሜ እና እሁድ ይጫወታሉ። እኚህ ሰው ረጅም ጊዜ የተጫወቱባቸውን ራኬቶች በየጊዜው ሰብስበው ለሳራሳቸው ትውስታ ያስቀምጣሉ። ታዲያ ይህች የጓደኛችን ሚስት ታዲያ አራዳ ነገር ነበረች እና ይህን ነገር በጊዜ ሂደት ጠንቅቃ ተረድታለች። ከተጋቡ በኋላ በነበረው የመጀመሪያ የገና ጊዜ የሚወዱትን ቆንጆ ራኬት ገዝታ ሰጠቻቸው። ከምንግዜም ምርጥ ራኬቶቼ ተርታ አስቀምጠዋለው ብለው ቁምሳጥናቸው ውስጥ አስገቡት። ልክም ይሁን አይሁን ሁላችንም የራሳችን የምንላቸው ፤ ልዩ ቦታ የምንሰጣቸው ነገሮች አሉን። የጓደኛችን አባት ቴኒስ መውደዳቸው ልክ ነበርና የራሴ ብለው ይዘውታል። የልጃቸው ሚስት ደግሞ የእኔ በሚሉት ነገር ገብታ ቀረበቻቸው። አልፎ አልፎ ይደውሉላታል። የገዛ ልጃቸው እስኪገረመው ድረስ ነው የሚወዷት። ቀስ በቀስ ቴኒስ አብራቸው እንድትጫወት ማድረግ ጀመሩ። እሳቸውም እንደእርሷ የቴኒስ መጫወቻ ሰጧት። እሷ የቴኒስ ወዳጅ ስላልነበረች ያን ያህል አልሳባትም። ነገር ግን በደስታ ተቀበለቻቸው። ለሚጫወቱበት የተራ እየከፈሉ አልፎ ያጫውቷታል። እናም እንደነዚህ አይነት አጋጣሚዎችን መጠቀም ብልጠት ነው ፤ ከሰው ጋር በፍቅር የመኖር ጥበብ ምልክት ነው።        



የሰጡሽን ብዪ ፤ ጠጪ   እንኳን የባልሽ ዘመዶች ቤት ሌላም ዘመድ ቤት ብትሄጂ ባትወጂም የግድ ማድረግ ያለብሽ ነገር ነው። ጠላ ባትጠጪም እነሱ ትጠጣ ብለው ከሰጡሽ መጠጣት አለብሽ የቀረበው ላንቺ ነውና! ምንም ሳታቅማሚ የሰጡሽንም መብላት ከዚህ ጋር አብሮ ይሄዳል።
አንድ በቅርብ የምናውቀው ሰው ተጫዋች ፤ ተግባቢ ነገር ነው። በሚስቱ ቤተሰቦች ግን የሚታየው እንደ አንድ ገገማ ፤ ባዶ ጉረኛ ሰው ነው። አይወዱትም። ምናልባት ልጅቷን ያገባት አባቷ ከሞቱ በኋላ መሆኑ ነው እንጂ ልጁ ከቤተሰቦቿ ጋር ባለው ግንኙነት ምክንያት በአባቷ ጋር ይጣላ ነበር ብሎ መደምደም ይቻላል። ልጁ የሚስቱ ቤተሰቦች ቤት ብዙ ግዜ አይሄድም። ድግስ ደግሰው ቢጠሩትም አይሄድም ፤ እሷን ልኮ የሚሄድበት ይሄዳል። ይሄ በጣም ያናድዳቸዋል። ንቆን ነው ወይም ለእኛ ግድ ስለሌለው ነው እንዲህ የሚያደርገው ይላሉ። ይባስ ብሎ ደግሞ ከስንት አንዴ እቤታቸው ሲሄድ እና የሚበላ ነገር ሲያቀርቡለት አይበላም። እንጀራው ይቆመጥጣል ፤ ወጡ ምስር ነው ወዘተ ይላል። የሚስቱ ቤተሰቦች ታዲያ ልጁን ከእነሱ የሚያገናኝ ነገር ሊያገኙ አልቻሉም። እሷንም ቀስ በቀስ እየገፏ ፤ እየገፏት መጥተዋል። ይሄ በጣም ጤናማ ያልሆነ ነገር ነው። ልጅቷም ከቤተሰቦቿ መጣላት የለባትም። ባሏ ቢያኖራት ፤ አብራው ብትተኛ ፤ የፈለገ ነገር ቢሆን በእሱ ግድየለሽነት ከቤተሰቦቿ ልትቆራረጥ አይገባም። እናቷም ለምን ትቀየማት?  እና እንደነዚህ አይነት ቀላል የሚመስሉ ነገሮች ውጤታቸው ከባድ ነው። ላወቀበት ሰው ጥልቅ ቁርኝት ሲፈጥሩ ላላወቀበት ደግሞ ያጣላሉ።


አትከራከሪያቸው! እንግዴህ የሰው ልጅ በየዘመኑ የራሱ ድክመቶች አሉበት። ኢትዮጵያውያንም ፤ አሜሪካውያንም ያው ናቸው። ተገቢ ያልሆነ ነገር የሚናገሩ ሰወቸ አይጠፉም። ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያየ የቋንቋም ፤ የባህልም ፤ የስነልቦናም ባህሪ ያላቸው ማህበረሰቦች አሉ። የአማራ እና የኦሮሞ ልጅ ወይም የትግሬ እና የኦሮሞ ልጅ ሊጋባ ይችላል። አንዲት ልጅ የገጠማትን ነገር በቅርቡ አጫውታኛለች። ከአገባች እና የባሏን ቤተሰብ ከተዋወቀች በኋላ የባሏን አባት ባህሪ ለመረዳት ጊዜ አልፈጀባትም። በአንድ የበአል ወቅት የባሏ አባት ዘረኛ ቀልድ ነገሯት እና ከት ብለው ሳቁ። ነገሩ ቢያናድዳትም እንደምንም ስሜቷን ችላ ፈገግ አለችላቸው። ሰውዬው እንግዴህ የኖሩበትን ነው የነገሯት። ኢትዮጵያም ውስጥ ሆነ የትም አለም ዘረኛ ቀልድ ፤ የእንዱን ማህበረሰብ ከሌላው ዝቅ የሚያደርግ ቀልድ የሚናገሩ ሰዎች አሉ። ያለ ነገር ነው ብለሽ እለፊው። ታሪኩን የነገረችኝ ልጅ ያደረግችው ይህንን ነው። ቀልዱ አያስቅም ፤ በዛ ላይ ዘረኛ ነው። ግን አልተከራከረቻቸውም ፤ ዝም ብላ ሰማቻቸው። አንቺም እንደዚህ አድርጊ! ምን አዳረቀሽ ፤ የባልሽ ቤተሰቦች የኖሩበት የራሳቸው ህይወት አላቸው። አንቺ የመጣሽው አሁን ነው። ከምንም በላይ የምትቀርቢው ደግሞ ልጃቸውን ነው ባልሽን ፤ እንጂ ሌላ ሰው አይደለም። ስለዚህ ምንም ይበሉ ምንም እንደማያውቁ አይነት አድርገሽ አትያቸው። በቃ ስሚያቸው! ሳቂላቸው! የባልሽ ዘመዶች የቤሮ ጓደኞችሽ አይደሉምን እና የምር ክርክር አያስፈልግም። የምርጫ 97 ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰዉ ሁሉ የሚያወራው ፖለቲካ ነበር። ባልና ሚስት በየወላጆቻቸው ጎራ ተሰልፈው መንግስት እና ተቃዋሚዎችን ይደግፉ ነበር። በቅርብ የምናውቃቸው ባልና ሚስትን ጉዳይ በአጭሩ እንንገራችሁ። ሚስት የመንግስት ፤ ባል የተቃዋሚዎች ደጋፊዎች ነበሩ። የሚስትየው ቤተሰቦችን ምርጫውን የመኖር እና የመሞት ያክል አክረው ስለተመለከቱት አባቷ ከልጃቸው ባል ጋር የሞት ሽረት ክርክር ያደርጋሉ። በስተመጨረሻ ነገሩ የምር መሆኑ የገባው የልጅቷ ባል የፖለቲካ ጉዳይ ሲነሳ ቶሎ በአጭሩ ሳይከራከር ይዘጋው ጀመር። ከዛ ሰላም ወረደ ፤ የኢሃፓ እና የመኢሶን አይነት ነገር በባል እና ሚስቶቹ ቤት አልተከሰተም። እንዲያው ከዛ በኋላ ሁለት ልጆች ወለዱ ፤ የልጅቷ አባትም በጠና ታመም ፤ ባሏ ብዙ ረድቷቸው አይቀሬው ሞት ወሰዳቸው። ልክ ነው ፤ የተጓዳኞቻችንን ቤተሰቦች በዚህ መንገድ ነው ልንቀርባቸው የሚገባው። እናም የገና ቀን ቡና ላይ ክርክር ከተነሳ ብዙ ክርክር ውስጥ አትግቢ! ያሉትን ፈገግ ብለሽ ተቀበዪ!       

እኔ አውቃለው ማለት እነሱ ላይ አይሰራም!  አስተማሪ ለመሆን መሞከር ተገቢ አይደለም። የባልሽ ወላጆች ያንቺም ወላጆች ናቸው። በእድሜ ብዙ ይበልጡሻል። ከእናንተ የበለጠ አውቃለው የሚል መንፈስ ብታሳዪያቸው ደስ አይላቸውም። የአንቺ እውቀት አንቺ ጋር ይሁን። በየንግግሮቻችሁ ጣልቃ ፤ በየእንቅስቃሴያችሁ መሃል እራስሽን እንደአዋቂ አድርገሽ አታቅርቢ።


የደበቁት መፅሃፍ ፤ ካሴት ፤ ሲዲ ውሰጂባቸው   የባልሽ ቤተሰቦች አሁን አርጅተው ቢገኙም እንደአንቺ በወጣትነታቸው ብዙ ቦታ ረግጠዋል። የባልሽ እናት በወጣትነት ዘመናቸው ያነበቡት እና እስከአሁን ድረስ ግን ከልጆቻቸው የደበቁት የወሲብ መፅሃፍ ካለ ለኔ ስጡኝ በያቸው። ከልብሽ እንደምትፈልጊው ንገሪያቸው! አሁን ቢያሳፍራቸውም ላንቺ ሲሰጡሽ ግን “ያኔ ልክ ነበርሽ እያለችኝ ነው የልጄ ሚስት” የሚል ስሜት ስለሚፈጥርባቸው ደስታ ይሰማቸዋል። እንዲሁ ሃይለኛ የፍቅር ፊልም ወይም ሙዚቃ ካሴት ከአላቸው ውሰጂባቸው ፤ የደስታ እና የእረፍት ፤ የአንድነት ስሜት ይሰማቸዋል።


ፊትሽ ይፈታ የባልሽ ቤተሰቦች ቤት ስትሄጂ የእንግድነት ስሜት ቢሰማሽ አይገርምም ቤትሽ አይደለምና። ግን ፈታ ለማለት ሞክሪ። ዝርክርክ ያለ ማድ ቤታቸው ፤ ያረጁት ሶፋዎቻቸው ፤ የድሮ የጣውላ ቴሌቪዥናቸውን እያየሽ ፊትሽ ሊጨማደድ አይገባውም። ፊትሽን ካነበቡት እንደውጭ ሰው ነውና የሚያዩሽ ላንቺ ጥሩ አይደለም። የድሮ ሰዎች አላስፈላጊ ክብር ይፈልጋሉ ፤ ነገር ያረዝማሉ ፤ ለእነሱ ዋጋ ያላቸው ነገሮች ላንቺ ምንም ላይሆኑ ይችላሉ። ነገር ግን ዝም ማለትን ወይ ፊትሽን ፈታ ማድረግ ልመጂ። የሆነ ሆኖ የባልሽ ወላጆች ናቸውና ካንቺ በስጋ ተነካክተዋል። የልጅሽ አያቶች ናቸው!





 

Post a Comment

Previous Post Next Post