"ከፍርሃቴ የተነሳ ማዘሬን ነበር በወቅቱ ያስደወልኩት"መስኡድ መሃመድ

how Ethiopian Midfielder Mesud Mehomed got his girl.

 ፍፁም ትሁት፣ አመለ ሸጋና ተግባቢ፣ የኢትዮጵያ ቡናው መስኡድ መሃመድ መገለጫዎች ናቸው፤ የሜዳ ውስጥ ድንቅ ችሎታው ደግሞ እጅግ ተወዳጅና ለአንድ ቡድን አስፈላጊው ሰው ያደርገዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቡና ቡድን አጨዋወት ያማረና የተመልካችን ቀልብ እንዲገዛ በማድረጉ በኩል መስኡድ መሃመድ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ትልቁን ቦታ ይይዛል፡፡ 
ከዳዊት እስጢፋኖስና ከፋሲካ አስፋው ጋር ያላቸው ጥምረት የኢትዮጵያ ቡናን የአማካይ ክፍል አስፈሪ ያደርገዋል፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ጎልተው ከወጡና በቀጣይ የመሃል ሜዳው ክፍል ኢንጅነር ይሆናሉ ተብሎ ከተመሰከረላቸው ተጫዋቾች አንዱ የሆነው መስኡድ መሃመድ ሁላችንም ከምናውቀው የሜዳ ላይ እንቅስቃሴው ውጭ ከሜዳ ውጭ / Off The Pitch/ ያለውን ሕይወቱን በመጠኑ ያስቃኘናል፡፡
*
*
*
-የእስልምና እምነት ተከታይ ብትሆንም የፋሲካ በዓልን ምክንያት አድርገህ ደውለህ እንኳን አደረሰህ ያልከው?
የሰፈሬ ልጅና ጓደኛዬ የሆነውን ጌድዮን ደረሰን ነው፤ በመጀመሪያ እንኳን አደረሰህ ያልኩት፡፡

-በህይወትህ ትልቅ ደስታን አገኘሁበት የምትለው ቀን?
በጣም የምወዳትን ባለቤቴን ሰብሪማ ኑር በሰርግ ያገባሁበትና የግሌ መሆኗን በይፋ ያረጋገጥኩበት ቀንና ኢትዮጵያ ቡና የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ አንስቶ ደጋፊው የተደሰተበትን ታሪካዊ ቀን፡፡

-በጣም ያዘንክበትስ?
ወላጅ አባቴን በሞት ያጣሁበት ቀን፡፡

-በዚህ ምድር ላይ ሆኖ ባላየውና ባልሰማው የምትለው?
ጦርነት የሚባል ነገር በምድራችን ላይ ባይኖርና ስለጦርነት ባልሰማ በጣም እመርጣለሁ፡፡

-ከእግር ኳስ ህጉች ቢቀየር ወይም ቢጨመር የምትለው?
የተጨዋቾች ቁጥር ቢቀነስ በጣም ደስ ይለኛል፡፡ ከዚህ ውጪ ቢጨመር የምለው ነገር የለም፡፡ ባለው ነገር እንዲሄድ ነው የምፈልገው፡፡

-የዘወትር የመዝናኛ ምርጫህ?
የአማርኛ ፊልምና ቲያትሮችን በመመልከት ነው ዘና የምለው፡፡

-አይተህ የወደድከው ፊልምና ያደነቅከው ተዋናይ?
ብዙ ፊልሞችን ነው የማየው፤ አሁን በቅርቡ ያየሁት የኔታ ፊልምን ግን በጣም የወደድኩት ሲሆን አርቲስቱን አለማየሁ ታደሰን ደግሞ በአተዋወን ብቃቱ በጣም ነው የማደንቀው፡፡

-አዳምጠህ የወደድከው ዘፈንና ድምፃዊ?
ለዘፈን ብዙም ፍቅር የለኝም፡፡

-በአይፖድህ ወይም በሞባይልህ አዘውትረህ የምትሰማው? 
ሀይማኖታዊ ይዘት ያላቸው መንፈሳዊ ነገሮችን ብቻ ነው የማዳምጠው፡፡

-አሁን የምትጠቀምበት የሞባይል አይነት 
ሳምሰንግ ኖት (NOTE)

-አሁን የምታሽከረክረው መኪና
ያሪስ፣ ቪትዝ

-ወደፊት ቢኖረኝ ባሽከረክረው ብለህ የምትመኘው መኪና?
ሬንጅ ሮቨርን ሁሌም እመኘዋለሁ፡፡

-ፋሽን ተከታይ ወይም ለፋሽን ቅርብ የምትባል ሰው ነህ?
አይደለሁም፡፡

-ምን አይነት አለባበስ ይመችሃል?
ሸሚዝ በጅንስ

-የምግብ ምርጫህ ወይም ለመመገብ ቅድሚያ የምትሰጠው 
ከዱባ በስተቀር ያገኘሁትን ምንም ሳልመርጥ እመገባለሁ በአጭሩ ያገኘሁትን እበላለሁ፡፡

-ከመጠጥ ጋር ያለህ ዝምድና?
ከሚጠጣ ነገር ውሀ በጣም ይመቸኛል፤

-ለመጀመሪያ ጊዜ የቆጠርከው ከፍተኛ ገንዘብ 
500ሺህ ብር ኢትዮጵያ ቡና ለፊርማ የሰጠኝ ገንዘብ ነው ያገኘሁት ትልቅ ገንዘብ፡፡

-መስዑድ ሀብታም ከሚባሉት ሰዎች ተርታ ይመደባል?
ጥሩ ነኝ አረ እንደውም አዎ

-አለኝ የምትለው ሀብት?
ዋናው ሰላምና ጤናዬ እንደሆነ ባውቅም የራሴ የሆነ ቢዝነስ ወይም ሀብት አለኝ ምንድነው ካልከኝ ግን አልነግርህም፡፡ 
አባካኝ ወይስ ቆጣቢ ከሚባሉት ተርታ ነው የምትመደበው?
አባካኝ የሚባለው የሚገልፀኝ ይመስለኛል፡፡ እኔና ቁጠባ በቅርበት አንተዋወቅም፡፡

-መስዑድ ራሱን በተመረጡ 3 ቃላቶች ይገልፅ ቢባል ራስህን እንዴት ነው የምትገልፀው?
ይሉኝታ የሚያጠቃው፣ ክፋትን የማይወድና የሚሸሽ ግን ደግሞ በጣም ደስተኛ የሆነ ሰው ነው ብዬ ነው ራሴን የምገልፀው፡፡

-ለመጨረሻ ጊዜ በአውቶብስ የሄድክበትን ቀን ታስታውሰዋለህ?
እ… አላስታውሰውም ግን ፕሮጀክት ስጫወት ሲ ሜዳ ለመሄድ ከሰፈሬ በስድስት ቁጥር ባስ እመላለስ ነበር፡፡

-በጓደኞችህ፣ በቤትህ ውስጥ ወይም በክለብህ ተለይተህ የምትጠራበትና የምትታወቅበት ቅፅል ስም አለህ?
ከዋናው ስሜ ቀጥሎ አረቦ በሚባለው ቅፅል ስሜ ነው የምታወቀው፡፡

-አረቦ ለምን ተባልክ?
በጣም ቀይ ስለሆንኩ አረቦ የሚል ቅፅል ስም ነው ሰፈሬ ውስጥ የወጣልኝ፡፡

-ከባህር ማዶ የምትደግፈው ብሄራዊ ቡድን?
በተለያየ ጊዜ የተለያየ ቡድን ነው የምደግፈው ዚነዲን ዚዳንን በጣም ስለምወደው በፊት ፈረንሳዮችን በጣም ነበር የምወዳቸው አሁን ግን ስፔኖች ልቤን አሸፍተውታል፡፡

-ከአሰልጣኞችስ?
የእኔ ምርጡ አሰልጣኝ ፔፕ ጋርድዮላ ነው፡፡

-ከተጨዋቾችስ?
የባርሴሎናው ዣቪ ለእኔ ምርጡና ልዩው ተጨዋች ነው፡፡

-በልጅነትህ እንደ እሱ ብሆን እያልክ አድንቀኸው ያደግከው ተጨዋች?
አንዋር ያሲን (ትልቁን) በጣም እያደነቅኩትና እየወደድኩት ነው ያደግኩት፡፡

-ለመጨረሻ ጊዜ ያነበብከው መፅሐፍ?
ብዙውን ጊዜ ጋዜጦችና መፅሔቶችን ነው በጣም የማነበው አጫጭር ነገሮች ላይ ነው ትኩረቴ፡፡

-አዘውትረህ የምትጠቀመው የተለየ ልምድ?
ከጨዋታ በፊትም ሆነ በኋላ እንዲሁም አንድ ነገር ከማድረጌ በፊት ሁሉንም ነገር ለአላህ በፀሎት እሰጣለሁ፡፡

-ጎል ስታስቆጥር ይበልጥ የምትደሰተው?
ሁሉም ቡድን ላይ ጎል ሳገባ በጣም እደሰታለሁ፤ በተለይ ብዬ የምመርጠው ቡድን የለም፡፡

-ሜዳ ላይ የሚያስቸግርህ ተጨዋች?
ልምምድ ላይ የእኛ ክለብ ተጨዋች የሆነችው ኤፍሬም ዘካሪያስ፡፡

-አብሬው ብጫወት በጣም ደስ ይለኛል የምትለው ተጨዋች?
ከዳዊት እስጢፋኖስ ጋር ኳስ እስከማቆም አብሬው ብጫወት በጣም ደስ ይለኛል፡፡ ከእሱ በተጨማሪ ከሳላህዲን ሰይድ ጋርም ብጫወት በጣም ነው የምደሰተው፡፡

-በጣም ስትበሳጭና ስትከፋ ምንድነው የምታደርገው?
ብስጭትና ንዴትን ለመርሳትና ለመረጋጋት ብቸኛ መሆንን ነው የምመርጠው፡፡

-በጣም ስትደሰት ደስታህን በምን መልኩ ነው የምታሳልፈው?
በደስታዬ ጊዜ የእኔ ናቸው ከምላቸው ጋር አብሬ መደሰትን ነው የምመርጠው፡፡

-ዋጋቸው የማይቀመስና ውድ የሆኑ ዕቃዎችን የመግዛት ልምድ አለህ?
በጣም ውድ የሆኑ ነገሮችን አልደፍርም፡፡ መካከለኛ ዋጋ ላይ ነው የማተኩረው አንዳንዴ ዋጋው ሳይሆን የዕቃው ጥሩነት ነው ይበልጥ የሚስበኝ፡፡

-መኖሪያ ቤትህ በድንገት ብንመጣ ምን ያህል ልብሶችና ጫማዎች አሉህ?
ዕውነት ለመናገር ቁጥር ስፍር የላቸውም፡፡ ቆጥሬያቸው ባውቅ ኖሮ ቁጥሩን እነግርህ ነበር፡፡

-አግብተሀል (ኒካ አስረሃል) 
አዎን፡፡

-የዛሬዋ የትዳር ጓደኛህን እንዴት አገኘሃት?
የዛሬዋን ባለቤቴን እንዳገኝ ጓደኛዬ ትልቅ ሚና ተጫውቷል እሱ ነው ያስተዋወቀኝ፡፡

-ለጋብቻ እንዴት ጥያቄ አቀረብክላት?
ጓደኛዬ ካስተዋወቀን በኋላ እኔ በጣም ፈራሁ በፍርሃት የተነሳ መደወል ሁሉ አልቻልኩም፡፡ ከፍርሃቴ የተነሳ ማዘሬን ነበር በወቅቱ ያስደወልኩት፡፡ የእኔን መጨነቅና መፍራት አይታ እናቴ ደውላ ስታናግራት ችግር የለም እሱ ራሱ ደውሎ ያናግረኝ አለች፡፡ በኋላ እንደምንም ደፍሬ ያበጠ ይፈንዳ ብዬ ደወልኩላት ከዚያ በኋላ እየተነጋገርን መጣን፡፡ በመጨረሻ አላህ ፈቀደ በአንድ ጣሪያ ስር አብረን መኖር ጀመርን ማለት ነው፡፡

-ባለቤትህን እንዴት ነው የምትገልፃት?
በጣም ቆንጆ፣ በጣም አስተዋይና በጣም ደግሞ ጨዋ የሆነች ሚስት ናት፡፡

-እንዲህ ላደነቅካት ባለቤትህ መጀመሪያ የሰጠሃት ስጦታ?
በገንዘብም ሆነ በወርቅ የማይተመነውን እኔነቴን፡፡

-የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች በመስዑድ አንደበት እንዴት ይገለፃሉ?
በእኔ እይታ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች የምርጦች ምርጥ ናቸው፤ ቡና እንድትጫወት የሚያደርጉህ እነዚሁ ምርጥ የሆኑ ደጋፊዎች በስቴድየም የሚያሳዩት አደጋገፍ ነው፡፡ ምርጦች ናችሁ እወዳችኋለሁ በልልኝ፡፡


By Hatri

Post a Comment

Previous Post Next Post